ከሦስት ሺሕ በላይ ተጠቃሚዎች የሚሳትፉት የ276 ሚሊዮን ዶላር የሊዝ ፋይናንስ ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ

ከሪፖርተር የወጣ መግለጫ
31 December 2017
ብርሃኑ ፈቃደ

ምንም እንኳ ፕሮጀክቱ ከሁለት ዓመት በፊት ቢጀመርም የዓለም ባንክና የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ባቀረቡት የ276 ሚሊዮን ዶላር ብድር አማካይነት ከ3,000 በላይ ተጠቃሚዎችን በማሽነሪ ኪራይ ብድር በአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ዘርፍ መሰማራት የሚችሉበትን ዕድል ይዞ ብቅ ማለቱ ይፋ ተደርጓል፡፡

ስለዚሁ ፕሮጀክት ትግበራ ሥራዎች የሚያብራራ የዓውደ ርዕይ ሐሙስ፣ ታኅሳስ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ተካሂዷል፡፡ ዘጠኙ ክልሎችና ሁለቱ የከተማ መስተዳድሮች የሚሳተፉበት ይህ ፕሮጀክት፣ እ.ኤ.አ. ከ2016 ጀምሮ በሚታሰብ ጊዜ እ.ኤ.አ. እስከ 2020 ድረስ እንደሚዘልቅ ታውቋል፡፡ ስለፕሮጀክቱ ትግበራ ከዓውደ ርዕዩ ቀደም ብሎ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫም የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ተቋቁሞለት፣ የፕሮጀክቱን ትግበራና ሒደት የሚከታተልና በበላይነት የሚመራ ኮሚቴ ተዋቅሮለታል፡፡

የዓለም ባንኩ የዓለም የልማት ማኅበር ቃል በገባው የ200 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ባቀረበው የ76 ሚሊዮን ዶላር ብድር፣ በጠቅላላው በ276 ሚሊዮን ዶላር በጀት ሥራ የጀመረው የአነስተኛ መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የፋይናንስ ትግበራ ፕሮጀክት፣ ከ276 ሚሊዮን ዶላሩ ውስጥ 269 ሚሊዮን ዶላሩ፣ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ በኩል ለማሽነሪ ግዥዎችና ለሥራ ማስኬጃ እንዲውል ተደርጎ ለ2,152 ኢንተርፕራይዞች እንደሚሠራጭ ያስታወቁት፣ በፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ኤጀንሲ፣ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ፋይናንስ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ወይዘሮ የመንዝወቅ ግረፌ ናቸው፡፡ ከዚህ ባሻገር በንግድ ሥራ ልማት ዘርፍ ለ912 ኢንተርፕራይዞች ለሚሰጠው ሥልጠና የ2.5 ሚሊዮን ዶላር በጀት መመደቡን ገልጸዋል፡፡

ፕሮጀክቱ እነዚህ ጨምሮ አራት ክፍሎች እንዳሉት ያብራሩት ወይዘሮ የመንዝወርቅ፣ ለብሔራዊ ባንክ አገልግሎት የሚውልና በማዕከል የሚመራ የኤሌክትሮኒክ ብድር ዋስትና ማስያዣ መመዝገቢያ (Centralized Electric Collateral Registry) የተባለው ሥርዓትም የፕሮጀክቱ አካል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ባንኩ ለሚያካሂዳቸው የኪሳራና የዕዳ መክፈል ችግሮች በሚያጋጥሙ ጊዜ አበዳሪዎች የሚከተሏቸው አሠራሮች የሚመረምርበትን ጥናት የሚደግፍ የ800 ሺሕ ዶላር ፋይናንስም የፕሮጀክቱ አካል እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በፕሮጀክቱ አስተዳደር ሥር ለተፅዕኖ ግምገማና ለኮሙዩኒኬሽን ሥራዎች 3.7 ሚሊዮን ዶላር መመደቡም ተጠቅሷል፡፡

ይህ ፕሮጀክት ያስፈለገበትን ምክንያት የኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አስፋው አበበ ሲገልጹ፣ እ.ኤ.አ. በ2014 የተደረገ ጥናት ያመላከተው ውጤት እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የፋይናንስ ጥናት፤›› በሚል ርዕስ የተካሄደው ይህ ጥናት፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ‹‹በመሀል የተዘነጉ›› ወይም ‹‹ሚሲንግ ሚድል›› መሆናቸውን አመላክቷል ብለዋል፡፡

የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ከአነስተኛ ገንዘብ አቅራቢ ድርጅቶች (ማይክሮ ፋይናንሶች) የፋይናንስ አገልግሎት ያገኛሉ፡፡ ትላልቅ ኢንተርፕራይዞችም ባንኮች ያግዟቸዋል፡፡ በመካከል የሚገኙት አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ግን የብድር አገልግሎት የሚሰጣቸው ተቋም እንደሌለና ተዘንግተው እንደቆዩ የጠቀሱት አቶ አስፋው፣ ይህ ችግር በተለይ ከ2007 ዓ.ም. ወዲህ ጎልቶ እንደመጣ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ከሁለት ዓመት በፊት በተደረገው የብድር ስምምነት መሠረት የ276 ሚሊዮን ዶላር (በወቅቱ ምንዛሪ ዋጋ የ7.5 ቢሊዮን ብር) በጀት የተያዘለት ማሽነሪ ኪራይ ፕሮጀክት ተነድፎ ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

የልማት ባንክ የሚያስተዳድረውን የማሽነሪ ኪራይ የብድር አቅርቦት በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት፣ የባንኩ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተሾመ አለማየሁ ናቸው፡፡ እንደ አቶ ተሾመ ማብራሪያ ተበዳሪዎች የሊዝ ፋይናንሲንግ ወይም የማሽን ኪራይ ብድር አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን የተቀመጡላቸውን መስፈርቶች ማሟላት ይጠበቅባቸዋል፡፡ አንደኛው በማሽነሪ ኪራይ መልክ ለሚበደሩት ገንዘብ የ20 በመቶ ቅድመ ክፍያ መፈጸም ይጠበቅባቸዋል፡፡

በዚህ መሠረት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሚሆኑት ከ500 ሺሕ እስከ 7.5 ሚሊዮን ብር ካፒታል ያላቸውና ከስድስት ሰው በላይ የሰው ኃይል የሚያስተዳድሩ አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞች ሲሆኑ፣ ከአንድ ሚሊዮን ብር ጀምሮ እስከ 30 ሚሊዮን ብር ድረስ ዋጋ ያላቸው ማሽነሪዎችን ከአገር ውስጥ አልያም ከውጭ አቅራቢያዎች በመግዛት፣ በማጓጓዝና በመግጠም እንዲቀርብላቸው የማድረግ ሥራ ልማት ባንክ የሚወጣው ኃላፊነት ይሆናል፡፡

የብድሩ አመላለስም ከአምስት ዓመት በላይ ባለው ጊዜ ውስጥ ሲሆን፣ ዘጠኝ በመቶ ወለድ እንደሚታሰብበትም አቶ ተሾመ አብራርተዋል፡፡ በዱቤ ግዥ ሥርዓት ለተጠቃሚዎቹ የሚቀርቡትን ማሽነሪዎች የስፔሲፊክሽን፣ የመወለዋወጫ፣ የጥገናና መሰል ጉዳዮችን በማስመልከት በምን አግባብ እንደሚያስተዳድር ከሪፖርተር የተጠየቁት አቶ ተሾመ፣ የማሽኖቹ ግዥ የሚፈጸም ዕቅድ ካላቸው፣ ማረጋገጫ ከሚገኝላቸውና እስካሁን ከተደረጉ ግዢዎችም ብቃታቸው የተረጋገጡ የውጭ አቅራቢያዎች መሆኑን፣ ባንኩ ከሚፈጽመው ባሻገር ተበዳሪዎች የሚያቀርቧቸው ሁኔታዎች ካሉም አብሮ መስፈርቶቹን እንደሚያዘጋጅ አብራርተዋል፡፡ እስካሁንም ከጃፓን ኩባንያዎች በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ስፌት ሥራዎች ለተሠማሩ ግዥ መፈጸሙን አብራርተዋል፡፡

የተጠየቀው የካፒታል መጠን ከፍተኛ ከመሆኑም ባሻገር፣ አብዛኞቹ አነስተኛና መካከለኛ የማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞች በሚቀርቡላቸው ማሽነሪዎች ጥራትና ብቃት ላይ ሥጋት እንዳላቸው ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ተሾመ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በአራቱ ዋና ዋና ክልሎች ውስጥ በአክሲዮን የተቋቋሙ የሊዝ ፋይናንስ ተቋማት እንዲህ ያለ ችግር ቢገጥማቸውም፣ ልማት ባንክ ከእነዚህ ትምህርት መውሰዱን ተናግረዋል፡፡ የማሽነሪዎቹ ጥናትና ብቃት ተረጋግጦና ተፈትሾ እንደሚቀርቡ ገልጸዋል፡፡

ባንኩ ባለው የውጭ ምንዛሪ ተጠቃሚነት ሳቢያ ከየትኛውም የውጭ አቅራቢ ድርጅት ያለ ውጣ ውረድ በቀጥታ ግዥ የሚፈጽመበት ዕድል እንደተሰጠው፣ ለሚያቀርባቸው ማሽነሪዎችም የጉምሩክና የተጨማሪ እሴት ታክስ ክፍያዎች እንደማይጠየቅ እሱም ደንበኞቹን እንደማይጠይቅ አቶ ተሾመ አስታውቀዋል፡፡

የዓለም ባንክና የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ የተሰጡት ብድር እንዳለ ሆኖ ልማት ባንክ ለፕሮጀክቱ የአምስት ዓመታት ቆይታ 41.5 ቢሊዮን ብር መመደቡን፣ ባለፈው ዓመት ከአሥር ቢሊዮን ብር በላይ ጥያቄ ማስተናገዱን፣ ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ መፍቀዱንና ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ መልቀቁን ወይም ማሽነሪዎች በመግዛት ማስረከቡን ጠቅሰዋል፡፡ ከአንድ ወር በፊት በአዳሪዎቹ ቃል ከተገባው ገንዘብ ውስጥ 12 ሚሊዮን ዶላር መለቀቁንም አቶ ተሾመ አስታውሰዋል፡፡

ምንም የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎችን የፋይናንስ አቅርቦት ችግር በዚህ መልኩ ለመፍታት መነሳቱን መንግሥት ቢያስታውቅም፣ የመሥሪያ ቦታ እንዲሁም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግሮች መሠረታዊ ማነቆዎች መሆናቸው አልቀረም፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪም አብዛኞቹ ኢንተርፕራይዞች የሕጋዊና የቴክኒክ ሰነዶች አቀራረብ ችግሮች እንደሚታዩባቸው ልማት ባንክ አስታውቋል፡፡ እነዚህን ለመፍታት ኤጀንሲው የኢንዱስትሪ ማምረቻ ቦታዎችን ለመገንባት የዲዛይን ሥራዎችን በማከናወን ለክልሎች ማሠራጨቱን አቶ አስፋው አስታውቀዋል፡፡